ጤና

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመጪው ክረምት የወባ በሽታ ሥርጭት እንዳይስፋፋ እየተሰራ ነው

By Adimasu Aragawu

June 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመጪዎቹ የክረምት ወራት የወባ በሽታ ሥርጭት እንዳይስፋፋ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

የክልል ጤና ቢሮ ምክትል እና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ÷ በክልሉ በክረምት ወራት የሚፈጠረውን የወባ ሥርጭት ለመቀነስ የዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

በተለይም ባለፉት 10 ወራት የወባ ሥርጭትን ለመከላከል የተከናወኑ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመገምገም ቀጣይ ሥራዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ መፈጠሩን ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ ባለፉት 10 ወራት የአጎበር አጠቃቀም እና ስርጭትን የማሳደግ እንዲሁም 312 ሺህ 913 ቤቶች የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት መካሄዱን ነው የጠቀሱት።

በተጨማሪም 980 ሺህ 464 የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የወባ በሽታ መከላከል፣ ሕክምና እና ምርመራ አገልግሎት የመስጠት ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።

በክልሉ ወባን የመከላከል ሥራ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው÷ በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ የግንዛቤ ፈጠራና የመከላከል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እየተደረገ እንደሆነም አስረድተዋል።

በክልሉ 82 በመቶ የሚደርሱ የሕብረተሰብ ክፍሎች የወባ ሥርጭት ባለባቸው አካባቢዎች እንደሚኖሩ አንስተው÷ ከፍተኛና መካከለኛ ደረጃ የወባ ሥርጭት ያለባቸውን በመለየት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በዚህም በክልሉ 59 ወረዳዎች 6 ሺህ 189 ቋሚ የወባ ትንኝ መራቢያ ሥፍራዎችን በመለየት 242 ሺህ 966 ካሬ ሜትር ላይ የጸረ እጭ ኬሚካል ርጭት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ 337 ሺህ 892 ካሬ ሜትር ጊዜያዊ የወባ ትንኝ መራቢያ ሥፍራዎችን ማዳፈንና ማፋሰስ ሥራዎች መሰራቱን አንስተው÷ከ197 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሥራው መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook WMCC TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!