አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቡሬ፣ ቡልቡላ እና ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለውን የኃይል አቅርቦት እጥረት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ አማካሪ አቶ ዳንኤል ኦላኒ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የመሰረት ልማት አቅርቦትን ማሟላት ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡
በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘንድ በስፋት የሚስተዋለውን የኃይል አቅርቦት እጥረት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የቡሬ፣ ቡልቡላ እና ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ እንዱስትሪ ፓርኮች በኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት በሙሉ አቅማቸው ሥራ መጀመር አለመቻላቸውን አንስተዋል።
መንግስት የአግሮ እንዱስትሪ ፓርኮችን የኃይል እጥረት ችግር ለመፍታት ውሳኔ ማሳለፉን ጠቁመው ÷ ለዚህም የሰብስቴሽኖችን ግንባታ ለማከናወን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ለሰብስቴሽን ግንባታ የሚያስፈልጉ ግበዓቶችን ከውጪ ለማስገባት 34 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተፈቅዶ ግዢ እየተፈጸመ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
አሁን ላይ 113 ኩባንያዎች በአግሮ እንዱስትሪ ፓርኮቹ ለመሰማራት የመግባቢያ ስምምነት የፈረሙ ሲሆን ÷ 31 በተለያየ ደረጃ ሥራ የጀመሩና 12 የሚሆኑት ደግሞ ወደ ምርት ማምረት የገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን በበኩላቸው ÷ በአግሮ እንዱስትሪ ፓርኮቹ የኃይል አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ለሚከናወነው የሰብስቴሽን ግንባታ የዲዛይንና ሌሎች ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የሰብስቴሽን እና የማስተላለፊያ መስመሮችን ግንባታ እንዲሁም ቀሪ ሥራዎችን ለማከናወን በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook WMCC TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!