የሀገር ውስጥ ዜና

የአፋር ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ተጀመረ

By Meseret Demissu

August 10, 2020

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 4 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በሰመራ ከተማ ተጀመረ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ÷ የክልሉን የ2012 በጀት ዓመት የስራ እቅድ አፈጸጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም በበጀት ዓመቱ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን አመላክተዋል።

በክልሉ ሰላምን በማስፈን ረገድ አበረታች ስራዎች መተግበራቸውንም አንስተዋል።

ከኢሳ ማህበረሰብና አጎራባች ክልሎች ጋር የህዝቦችን አብሮነትና የሰላም እሴት ግንባታ ለማጠናከር የተካሄደው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኮች ውጤት ማስገኘታቸውንም ገልጸዋል።

በድንበር አካባቢ በተካሄደው ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ቁጥጥር ስራ 71 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ና ከ81 ሺህ በላይ ጥይቶች ተይዘዋልም ነው ያሉት።

በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሁም ለአርብቶ አደሩ ልጆች ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች እንደነበሩም አንስተዋል፡፡

ከሰባት ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የቤት እንስሳት ክትባትና ህክምና መሰጠቱንም ገልጸዋል።

ጉባኤው በሶስት ቀናት ቆይታው የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ሪፖርት እንዲሁም በክልሉ የ2013 የስራ ዘመን በጀት ዙሪያ በመምከር  ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።