አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕንድ አሕመዳባድ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ በተከሰተው የአውሮፕላን አደጋ 204 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ አንድ ሰው በሕይወት መትረፉ ተሰምቷል፡፡
ዛሬ ጠዋት ቦይንግ 787-8 የሚል ስያሜ ያለው አውሮፕላኑ በምዕራብ ሕንድ አሕመዳባድ አውሮፕላን ማረፊያ ምድር እንደለቀቀ ብዙም ሳይጓዝ መከስከሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የአካባቢውን ፖሊስ ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው÷ አውሮፕላኑ ከተነሳ ከ30 ሴኮንዶች በኋላ ነው የተከሰከሰው።
በአደጋው እስካሁን የ204 ሰዎች አስከሬን መገኘቱንና የአንድ የእንግሊዝ ዜግነት ያለው ግለሰብ በህይወት መትረፉ ተገልጿል፡፡
በአደጋው የቀደሞው የሕንድ ጉጂራት ግዛት ሚኒስትር የነበሩት ቪጃይ ሩፓኒ መሞታቸው ሲረጋግጥ÷ አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት አካባቢ የነበሩ 50 የሚዲካል ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና መወሰዳቸው ተመላክቷል፡፡
አደጋውን ተከትሎ በረራዎች የተቋረጡ ሲሆን÷ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው፡፡
የአውሮፕላን አደጋው ምክንያት እስካሁን እንዳልተገለጸና የእንግሊዝ እና አሜሪካ የአደጋ ልዑካን ሁኔታውን ለማጣራት ወደ ሙምባይ ማቅናታቸው ተሰምቷል፡፡
በአውሮፕላኑ ውስጥ 169 የሕንድ፣ 53 የብሪታንያ፣ 7 የፖርቹጋል፣ አንድ የካናዳ እና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ተሳፍረው እንደነበርም ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል፡፡
በሚኪያስ አየለ