የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ መኖሪያ ቤቶችን በፍጥነትና በጥራት ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Melaku Gedif

June 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤቶችን በፍጥነትና በጥራት በተለያዩ አማራጮች ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ከንቲባዋ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ጀርመን አደባባይ አካባቢ በመንግስት እየተገነቡ የሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች የደረሱበትን ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም በአዲስ አበባ የነዋሪዎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት በተለያዩ አማራጮች የመኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በመንግስት፣ በግሉ ዘርፉ እንዲሁም በመንግስትና በግል አጋርነት መኖሪያ ቤቶችን በጥራትና በፍጥነት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የመሬት አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኛ እንደሆነ አጽንኦት መስጥታቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ሚኤሳ ኤሌማ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

በጀርመን አደባባይ አካባቢ እየተገነቡ የሚገኙት መኖሪያ ቤቶች ከተጀመሩ 9 ወራት ማስቆጠራቸውን ጠቁመው÷ ግንባታው በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ተጨማሪ የቤት ግንባታ ሥራ የማከናወኑ ሒደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በቤት ግንባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ የግል አልሚዎች የቤት አቅርቦት መጨመርን ግምት ውስጥ በማስገባት የጀመሩንት ግንባታ በፍጥነት እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል መሬት አጥረው ግንባታ ያልጀመሩ አልሚዎች በፍጥነት ሥራ በመጀመርና ግንባታውን በማጠናቀቅ ለቤት ፈላጊዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!