ስፓርት

ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ …

By Hailemaryam Tegegn

June 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በርካታ ጀግና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም ላይ በሚያደርጓቸው ውድድሮችና በሚያመጧቸው ውጤቶች የሀገራቸውን ህዝብ በደስታ ዕንባ አራጭተዋል፤ ስሜትን ከፍ ዝቅ የሚያደርጉ በርካታ አኩሪ ገድሎችንም ሰርተዋል፤ እየሰሩም ይገኛሉ።

ነገር ግን እርሱ ከሁሉም ልዩ ነው ትውልድ ከትውልድ የሚቀባበላቸው ዘመን ተሻጋሪ የጀግንነት እና የአሸናፊነት ታሪኮችን በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ጽፏል፤ የጀግንነቱን ግማሽ ያህል እንኳን ያልተዘመረለት ነው ቀነኒሳ በቀለ፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ካደረጉ ጀግና አትሌቶች መካከል በግንባር ቀደምነትም ይጠቀሳል፡፡

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በመሮጫ ትራኩ ላይ ከተገኘ ኢትዮጵያ ወርቅ እንደምታገኝ ብዙዎች እርግጠኛ ሆነው ውድድሩን ይመለከታሉ፤ እሱም በተደጋጋሚ ውድድሮችን በበላይነት በማጠናቀቅ ኢትዮጵያውያንን የሚፈልጉትን የቀዳሚነት ስፍራ ባለማስነካት አኩርቷቸዋል።

ለኢትዮጵያ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በርካታ ወርቅ ያመጣ ሲሆን፤ በግል ውድድሮች ካገኛቸው ድሎች በላይ ለሀገር ያሳካቸው ድሎች ይበልጣሉ፡፡

አትሌት ቀነኒሳ ለሀገሩ ኢትዮጵያ 24 የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል፤ የሰበሰባቸው የወርቅ ሜዳሊያዎች ብዛት ብዙ ሀገራት አንድ ላይ ተደምረው ማምጣት የማይችሉትን ነው፡፡

ከበቆጂ ተነስቶ የሚሊየኖች ተምሳሌት ሆኖ ከትራክ እስከ ሀገር አቋራጭ ከዚያም በማራቶን የደመቀው ቀነኒሳ፤ በስብዕናውም ይወደዳል።

በአትሌቲክሱ ዓለም ባሳካቸው ገድሎች ከዘመን ዘመን የሚወሳ፣ ኢትዮጵያ የምትኮራበት እና ትውልድ ሊማርበት የሚገባው ጀግና ነው፡፡

የአትሌት ሀይሌ ገብረስላሴን ፈለግ እንደተከተለ የሚነገርለት ቀነኒሳ በቀለ፤ የመጨረሻ ዙርን ልክ እንደ አጭር ርቀት የሚሮጥ፣ በአትሌትነት ዘመኑ በሰራቸው ታሪኮች ስሙን በወርቅ ቀለም ማስፈር የቻለ የኢትዮጵያ ውድ ልጅ ነው።

የኢትዮጵያ የምንግዜም ምርጡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ዛሬ 43ኛ ዓመት የልደት በዓሉ ነው፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ