የሀገር ውስጥ ዜና

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው

By Abiy Getahun

June 14, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኮሪደር ልማት ሥራ የ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የኮንትራት ስምምነት በመፈጸም እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊና የኢንዱስትሪና ከተማ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በሰባት የክልሉ መቀመጫ ከተሞች 165 ኪሎሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡

የኮሪደር ልማት ሥራው በቡታጅራ፣ ሆሳዕና፣ ዱራሜ፣ ወልቂጤ፣ ወራቤ፣ ሳጃ እና ቁሊቶ ከተሞች እየተከናወነ መሆኑን አንስተው÷ ሥራው በሁለት ምዕራፍ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ 115 ኪሎ ሜትር ለመስራት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንም ገልጸው፤ ቀሪው 50 ኪሎ ሜትር ሥራ በሁለተኛው ምዕራፍ ይሰራል ብለዋል።

ሥራው የተሟላ የኮሪደር ልማት መስፈርቶችን በማሟላት እየተከናወነ በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በኮሪደር ልማት ሥራው ኅብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲሳተፍ ግንዛቤ በመፍጠር በቂ ዝግጅት በመደረጉ ተሳትፎው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

የገቢ ማሰባሰቡ በክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ እንዲመራ በማድረግ ኅብረተሰቡ በጥሬ ገንዘብ ከመደገፍ ባሻገር የኮሪደር ልማቱ የሚነካቸውን ቦታዎች በፍጥነት ምቹ በማድረግ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በበጎ ፈቃደኝነት መደገፉን ተናግረዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ሥራ በቀጣይ በክልሉ ሁሉም ከተሞች እንደሚከናወን የገለጹት አቶ ስንታየሁ÷ በትላልቅ ከተሞች ላይ የግንባታ ሥራዎችን ጭምር በማካሄድ እንደሚሰራና በሌሎች የማዘጋጃ ከተሞች ጽዳትን ከማስጠበቅ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ አመልክተዋል፡፡

በከተሞች የሚሰሩ ሥራዎች በመሰረተ ልማት መናበብ የሚሰሩ በመሆናቸው በተለይም ከውሃ፣ መብራት ኃይልና ቴሌኮሙኒኬሽን ተቋማት ጋር ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተሞችን ውብ እና ምቹ የሚያደርጉ በመሆናቸው የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!