አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግለሰቦቸ እና ተቋማት ራሳቸውን ከሳይበር ጥቃት እንዲከላከሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) አሳስቧል፡፡
በአስተዳደሩ የተቀናጀ የሳይበር መከላከል አገልግሎት ዲቪዥን ሃላፊ አቶ አቤል ተመስገን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እየተስፋፋ መሆኑን ተከትሎ የሳይበር ጥቃቶች ውስብስብ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ ጠቅሰው ÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 7 ሺህ 514 የጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ጥቃቶች አብዛኞዎቹ በግለሰብ እና ተቋማት ላይ የተሞከሩ መሆናቸውን ያስረዱት ሃላፊው ÷ ግለሰቦቸ እና ተቋማት ራሳቸውን ከሳይበር ጥቃት መከላከል የሚያስችል ግንዛቤ እና አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በተለይም ግለሰቦች በቴሌግራም የሚላኩ ያልታወቁ ሊንኮችን ባለመክፈት፣ የይለፍ ቃላቸውን በማዘመን እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚተላለፉ ሀሰተኛ ምስሎችንና መረጃዎችን በመለየት ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም እንደ ማህበራዊ ሚዲያው አይነት የሚጠይቀውን መረጃ በማሟላት ባለ ሁለት አሃዝ የማረጋገጫ ኮዶችን መጠቀም ችግሩን መከላከል እንደሚያስችል ነው የገለጹት፡፡
በዚህ ረገድ ኢንሳ ለባለሙያዎች እና ተቋማት በርካታ የሳይበር ጥቃት መከላከል ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመው÷ግለሰቦችና ተቋማት ከኢንሳ ጋር በትብብር እየሰሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ግለሰቦች መሰል የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን በሚመለከቱበት ጊዜም በ933 ነጻ የስልክ መስመር ደውለው ሪፖርት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ