የሀገር ውስጥ ዜና

ሆስፒታሉ ሰው ሰራሽ እግር በማምረት ታካሚዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው

By Mikias Ayele

June 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሰው ሰራሽ እግር በማምረት ታካሚዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አይንሸት አዳነ ለፋና ሚድያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት ÷ በሆስፒታሉ ሰው ሰራሽ እግር የማምረቱ ሒደት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የማምረቻ ማዕከሉ ባለፉት ወራት ለተለያዩ ታካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ አጋር አካላት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከ6 ወራት በፊት የተቋቋመው ማዕከሉ ÷ በቀጣይ ሰው ሰራሽ እጅ ለማምረት ጥረት እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ሆስፒታሉ በቀን 200 ሲሊንደር ኦክስጅን ማምረት የሚያስችል ማዕከልን ወደ ሥራ ማስገባቱን ነው ያስረዱት፡፡

ከአማራ ክልል ባለፈ ለአጎራባች ክልሎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የካንሰር ማዕከል ሥራ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማሕበረሰብ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

በምናለ አየነው