አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ4 ቢሊየን ብር ወጪ ያስገነባቸውን 22 ፕሮጀክቶች መርቀው ከፍተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሀገራዊና ተቋማዊ ራዕይን በማሳካት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲ የ70 ዓመታት የላቀ የማስተማርና የምዕተ ዓመት የአገልግሎት ጉዞውን በሚዘክርበት ዕለት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መርቀን ከፍተናል ብለዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የካንሰር የጨረር ሕክምና ማዕከል፣ የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻ ፕላንት፣ ሰው ሰራሽ እግር ማምረቻ፣ የቅድመ ሕክምና ቤተ ሙከራና የማህበረሰብ ት/ ቤቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ከምርጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት፣ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማዘመንና የላቀ ትውልድና ሀገር ግንባታ አሻራውን እንዲያኖር ጉልህ አበርክቶ ይኖራቸዋል ነው ያሉት፡፡
ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያን እንዲሁም የጎንደርን የታሪክ፣ የጥበብ፣ የሥልጣኔ እና የትምህርት ማዕከልነት ማሳያነቱን በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማሕበረሰብ አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን(ዶ/ር ) በበኩላቸው ÷ሆስፒታሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለአካባቢውን ማህበረሰብ በርካታ የጤና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የተገነቡ 22 አዳዲስ ፕሮጀክቶች 4 ቢሊየን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው ጠቁመው÷ፕሮጀክቶቹ ተጀምረው እስከሚጠናቀቁ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ የላቁ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ራስ ገዝ ለመሆን ዝግጅቱን አጠናቅቋል ነው ያሉት።
በሙሉጌታ ደሴ