አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሄራዊ ፈተና ከስርቆት በጸዳ መልኩ እንዲሰጥ በማድረግ ውጤታማና ተወዳዳሪ ትውልድ መፍጠር ይገባል አሉ።
የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ሂደትን በተመለከተ የጸጥታ ዕቅድና ኦሬንቴሽን መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የስራ ኃላፊዎች፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የክልልና ከተማ መስተዳድሮች ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ተወካዮች እና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የ12ኛ ክፍል ፈተና በአግባቡ እንዲሰጥ ትኩረት የተሰጠው የተሻለ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር መሆኑን ገልጸው፤ ፈተናውን ከስርቆት በጸዳ መልኩ እንዲሰጥ በማድረግ ውጤታማና ተወዳዳሪ ትውልድ መፍጠር ይገባል ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ችግሮችን በማረም ፈተናውን በተሻለ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የጸጥታ አካላት ሚና ትልቅ መሆኑን ጠቁመው፤ 12ኛ ክፍል ፈተና ከነበረበት ችግሮች ተላቆ በተሻለ መልኩ እንዲሰጥ የጸጥታ ተቋማት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘንድሮ ፈተናው ለ150 ሺህ ተማሪዎች በኦንላይን እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ፈተና አሰጣጡ ወደ ዲጂታል እንዲሸጋገር እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ ፖሊስ የ12ኛ ክፍል ፈተና በሰላም እንዲካሄድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሥነምግባር የታነጸ ትውልድ ለሀገር ሰላም ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፤ በፈተና አሰጣጥ ሂደቱ የጸጥታ ተቋሟት መሳተፍ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!