ቢዝነስ

የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አ.ማ የቡና የወጪ ንግድን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ተጨማሪ ኮንቴነሮች አቀረበ

By Hailemaryam Tegegn

June 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በመጪዎቹ ወራት የቡና እና የጥራጥሬ ምርቶችን የውጭ ንግድ ለማቀላጠፍ የሚያግዙ 104 ባለ 20 ጫማ ኮንቴነሮችን አቅርቤያለሁ አለ የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር፡፡

አክሲዮን ማህበሩ ከሜዲትራኒያን የባህር ትራንስፖርት ኩባንያ ጋር በመተባበር ኮንቴነሮቹን ከጅቡቲ ወደብ ወደ እንዶዴ ባቡር ጣቢያ ማጓጓዙን አስታውቋል፡፡

የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አ.ማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ኮንቴነሮቹ የቡና ላኪዎች ምርቶቻቸውን በዓለም ገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችሏቸው ገልጸው፥ በቀጣይም ተጨማሪ ኮንቴይነሮችን ለማቅረብ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የባለ 20 ጫማ ኮንቴነሮች አጥረት በመኖሩ ከጅቡቲ ወደብ በማምጣት ለላኪዎች መቅረቡን በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አ.ማ የግሎባል ሎጂስቲክስ ዳይሬክተር ወ/ሮ ምንተስኖት ዮሐንስ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በተለይም የቡና ምርት ጥራቱን ጠብቆ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ፣ የቅሸባ እና የጥራት መቀነስ እንዳይከሰት በሀገር ውስጥ ታሽጎ እንዲወጣ መመሪያ መቀመጡን አንስተዋል፡፡

የኮንቴነሮቹ መቅረብ ላኪዎች በጅቡቲ ወደብ የኮንቴነር አገልግሎት ለማግኘት የሚባክንባቸውን ጊዜና ወጪ ያስቀራል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ያለ ኮንቴነር ወደ ወደብ በሚጓጓዙበት ወቅት በሚያጋጥም የጥራት መቀነስና ቅሸባ የተነሳ ላኪዎች ለተጨማሪ ወጪ እንዳይዳረጉ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በኃይለማርያም ተገኝ