የሀገር ውስጥ ዜና

የመንግስትን ስም የሚያጠለሹ ጽሑፎችና መልዕክቶች ያሰራጨው ግለሰብ በ7 ዓመት እስራት ተቀጣ

By Adimasu Aragawu

June 18, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማህበራዊ ሚዲያ የመንግስትን ስም የሚያጠለሹ እና ራሱን የአማራ ፋኖ ብሎ የሚጠራውን ጽንፈኛ ቡድን የሚደግፉ ጽሑፎች እና መልዕክቶች በማሰራጨት የሽብር ተልዕኮ ሲፈፅም የነበረ ግለሰብ በሰባት ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ።

የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሽ ወንድማገኝ በርገና በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ሀ፣ ለ እና ሐ ድንጋጌ በመተላለፍ የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያመላክታል።

ተከሳሹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሀሳቡ፣ በወንጀል ድርጊት እና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን መንግስትን በጦርነት ከስልጣን ለማስወገድ አስቦ በህገወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ በመታጠቅ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባት እየተዋጋ ያለውና ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራ የጽንፈኛ ቡድን የፕሮፖጋንዳ ክንፍ በመሆን “በርገና ወንድማገኝ” የሚል የዋትስአፕ አካውንት ከፍቶ ነበር፡፡

የቡድኑ ልሳን ለሆኑ በዋናነትም ዘመድኩን በቀለ ለተባለ ግለሰብ በየካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ለቡድኑ የፕሮፖጋንዳ ሥራ ግብዓት የሚሆኑ በአርባ ምንጭ ከተማ መንግስት ቤት እያፈረሰ ነው የሚል መልዕክት እንዲሁም በየካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም የመንግስትን ሥርዓት ለመገርሰስ ብቸኛው አማራጭ የትጥቅ ትግል ነው የሚል መልዕክት ማስተላለፉ በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ ተገልጿል፡፡

‘እኔም አንዱ የዛ አካል ነኝ፤ ፋኖን እደግፋለሁ ሁሉም ሰው የድርሻውን ሊወጣ ይገባል’ የሚል እና ‘ሥርዓቱን በተለያዩ አማራጮች ማዳከም አለብን’ የሚል መልዕክት በቪዲዮ ቀርጾ ለዘመድኩን በቀለ እንደላከ ተገልጿል።

ወንድማገኝ ገብሬ በሚል ስም በተከፈተ የቲክቶክ አካውንት ላይ የተገለጹትን የፕሮፖጋንዳ መልዕክቶች በቪዲዮ አሰራጭቶ ከ10 ያላነሱ ሰዎች የተመለከቱት የመንግስትን ስም የሚያጠለሹ ተግባራትን ሲፈጽም ነበር።

እንዲሁም ራሱን የአማራ ፋኖ ብሎ የሚጠራውን ጽንፈኛ ቡድን አመራሮች ፎቶ በመለጠፍ እንዲሁም ማንነታቸው ያልታወቁ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦችን ፎቶ በመለጠፍ ጦርነትን የሚያባብሱ የተለያዩ መልዕክቶችን በማሰራጨት እንዲሁም ወጣቱን ለጦርነት የሚያነሳሱ መልዕክቶችን በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት እንዲሰራጩ በማድረግ ወንጀል ተከሷል፡፡

ግለሰቡ የፕሮፖጋንዳ ስራ በመስራት በመንግስት ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠርና የጠላት አላማ እንዲሳካ የተለያዩ የፕሮፖጋንዳ መልዕክቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲያሰራጭ የነበረ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ እያለች የጠላት ዓላማን ለማሳካት በማሰብ የጠላትን ጥቅም በሚያራምድ የፕሮፖጋንዳ ስራ ውስጥ በመሳተፍ ጠላትን የደገፈ በመሆኑ በፈጸመው ጠላትን መተባበር ወንጀል ተከሷል፡፡

ተከሳሹ በአጠቃላይ አመጽ ቀስቃሽ የሆኑ በርካታ የፕሮፖጋንዳ መልዕክቶችና ቪዲዮዎች ሲያጋራ እና ሲያነሳሳ እንደነበር የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ ክዶ በመከራከሩ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።

በዚህም መሰረት ተከሳሹ የቀረበበትን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር ወንጀል ችሎት ተከሳሹ በ7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

በመቅደስ ከበደ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!