ቢዝነስ

7ኛው ‘አግሮ ፉድ’ የንግድ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

By Abiy Getahun

June 19, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና፣ ጀርመን፣ ሕንድ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ቱርክ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ 16 ሀገራት የተሳተፉበት 7ኛው ‘አግሮ ፉድ’ የንግድ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደውን ዓውደ ርዕይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ ሃሰን መሃመድ፣ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር በርክ ባራን እና በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ዣንዲር ፌሬራ ዶስ ሳንቶስ አስጀምረዋል።

አቶ ሃሰን መሃመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ የአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየሰራች ነው።

ለዚህም የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ባለሃብቶች በዘርፍ እንዲሰማሩ እየተደረገ ነው ብለዋል።

መርሐ ግብሩ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ድርጅቶች የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ከሀገራቱ ከ156 በላይ ድርጅቶች በዓውደ ርዕዩ ላይ በመሳተፍ ምርት እና አገልግሎቶቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል።

የግብርና፣ የምግብና መጠጥ ግብዓቶች እንዲሁም የፕላስቲክ፣ ሕትመትና የማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችና ሌሎች ምርቶች በዓውደ ርዕዩ ቀርበዋል።

ዓውደ ርዕዩን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የጀርመኑ ፌርትሬድ እና ፕራና ኢቨንትስ በትብብር አዘጋጅተውታል።

በመላኩ ገድፍ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!