አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላት ሃላላ ኬላ ሪዞርት ታሪካዊና ዘመናዊ የግንባታ ጥበብ የተሰናሰሉበት አስደናቂ የዓለም አቀፍ የመስህብ መዳረሻ ነው አሉ።
በሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የተወያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላት የሃላላ ኬላ ሪዞርት ኢኮ-ቱሪዝም እና የጊቤ-3 የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ጎብኝተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታና የምርጫ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አሸብር ታደሠ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት መስራት የሚቻልበት አዲስ የፖለቲካ ባህልና ምኅዳር ተፈጥሯል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም ሃላላ ኬላን ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ የኢኮኖሚ አቅም እንዲሆኑ ተደርጓል።
የሃላላ ኬላ ኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻ ሪዞርትም ታሪክን በመጠበቅ ዘመናዊ የግንባታ ጥበብ የታከለበት ግዙፍ የልማት አቅም መሆኑን ተናግረዋል።
የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳዊት ገበየሁ እንዳሉት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተገነባው የሃላላ ኬላ ሪዞርት የተደበቀውን ታሪክ የገለጠ የመስህብ መዳረሻ ነው።
ሪዞርቱ ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር እና ለቱሪዝም መነቃቃት ወርቃማ ዕድል በማምጣት የኢኮኖሚ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ገለታ ኃይሉ፥ ሪዞርቱ ጸጋን በመለየት የቱሪዝም አቅም የሚሆኑ የልማት ስራዎችን ለመፍጠር ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል።
የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ሀጂ እስማዔል መሀመድ፤ የተገነቡና በግንባታ ሂደት የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።
ሪዞርቱ ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶችን በመንከባከብና በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላላፍ ዕድል የፈጠረ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የወጣቶች ክንፍ ምክትል ሰብሳቢና የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የወጣቶች ክንፍ ኃላፊና የሥራ አስፈፃሚ አባል ጥጋቡ ደጀኔ፤ ሪዞርቱ ታሪክና ዘመናዊ የግንባታ ጥበብ ተሰናስለው የተገለጡበት ድንቅ የመስህብ መዳረሻ ነው ብሏል።
ለደቡብ ኢትዮጵያ ቀጣና የቱሪዝምና አገልግሎት ዘርፍ ልማት መነቃቃት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑንም ተናግሯል።
በጋምቤላ ክልል የኢዜማ ምክትል መሪ ጋትቤል ቦል፥ ሪዞርቱ ለአካባቢው የቱሪዝም ልማት ከፍተኛ አቅም መፍጠሩን መመልከታቸውን አንስተዋል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!