የሀገር ውስጥ ዜና

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከአዘርባጃን ልዑካን ጋር ተወያዩ

By Hailemaryam Tegegn

June 20, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከአዘርባጃን የፐብሊክ ሰርቪስ እና ማኅበራዊ ፈጠራ ተቋም ሊቀ መንበር ኦልቪ ሜዲዬቭ እና ከአዘርባጃን አምባሳደር ሩስላን ናሲቦቭ ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እና በተለያዩ ዘርፎች በጋራ እና በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

ከውይይቱ በኋላ የአዘርባጃን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ይህን አገልግሎት በማስጀመር የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለማዘመን እና ለማቀላጠፍ እያከናወነች ያለችው ተግባር የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ሊቀ መንበሩ እና የአዘርባጃን አምባሳደር በብሔራዊ ቤተመንግሥት በመገኘትም የኢትዮጵያን ታሪካዊ እሴቶች የሚያሳየውን ሙዚየም ጎብኝተዋል።

በዚህ ስፍራ የተመለከቷቸው ነገሮችም ዕጅግ አስደናቂ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በለይኩን ዓለም