አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ሀገር በቀል እሳቤዎችን በማፍለቅ ለፓን አፍሪካኒዝም መጠናከር የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው አሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)።
የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው አርዳ የፖሊሲ ንግግር መድረክ ላይ “ፓን አፍሪካኒዝምን ማጠናከር” በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።
አፍሪካውያን ኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ በተቀዳጀችው ድል በመነሳሳት የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን በማቀጣጠል የራሳቸውን ሉዓላዊነት ማወጅ መቻላቸውን አውስተዋል።
የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ተቋማት እንዲቋቋም ማስቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ለፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ እድገት ታሪክ የማይዘነጋቸው ትላልቅ አሻራዎች ማኖሯን ገልጸው፤ ዛሬም ቀጥላለች ብለዋል፡፡
በተለይም ከለውጡ ወዲህ በመደመር እሳቤ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ሀገር በቀል የሪፎርም ሥራዎች ለፓን አፍሪካኒዝም መጠናከርና ለአህጉራዊ ብልፅግና ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው የተግባር ማሳያዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ለዚህ ዘመን የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ማደግ ገንቢ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም ነው ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ያነሱት፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተቋማዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች እንዳሉበት ገልጸው፥ አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካዊ እውቀትና ጥበብ እንዲፈቱ የተጀመረው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።
ድህነት፣ ኋላ ቀርነት እና የእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ተፅዕኖ ፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄን እየፈተኑ እንደሆነ ጠቅሰው፥ የአፍሪካ የትምህርት ስርዓት በአፍሪካውያን ባህልና እሴት መሰረት መቀረፅ እንዳለበት ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡