ቢዝነስ

ነዳጅ እያለ ዋጋ ይጨምራል በሚል እሳቤ የለም በሚሉ ማደያዎች መንግሥት ተከታትሎ እርምጃ ይወስዳል – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

By Adimasu Aragawu

June 21, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ነዳጅ እያለ ዋጋ ይጨምራል በሚል እሳቤ የለም በሚሉ ማደያዎች ላይ መንግሥት ተከታትሎ እርምጃ ይወስዳል አሉ።

አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ ይጨምራል በሚል አገልግሎት ያቆሙ መኖራቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ÷ በነዳጅ ላይ የሚጨመር ዋጋ አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

መንግስት ከግንቦት ወር ጀምሮ ከነዳጅ ድጎማ መውጣቱን ጠቅሰው÷ የነዳጅ ዋጋም በዓለም የነዳጅ ገበያ እንደሚወሰን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ወንድሙ ፍላቴ እንዳሉት÷ ነዳጅን በተመለከተ መንግስት ከድጎማው እንዳልወጣና ተጨማሪ የታክስ ክፍያዎችን እንደሚተገብር በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች የተሳሳቱ ናቸው።

የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ተከትሎ በነዳጅ ማደያዎች ላይ ያልተገባ ወረፋ እየተስተዋለ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ሕብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያዎቹ የሚናፈሰው ከእውነት የራቀ አሉባልታ መሆኑን እንዲገነዘብ አሳስበዋል።

የድጎማም ሆነ የታክስ ክፍያ እንደማይኖርና ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት በሀገር ውስጥ ያለውን የነዳጅ ዋጋ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ያደርግ የነበረውን የጥቅል ድጎማ በሂደት በመቀነስ እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም መጨረሻ ከድጎማ ሥርዓት በመውጣት በዓለም ገበያ ልክ እንዲሆን አድርጎ ነበር፡፡

ሆኖም መንግስት ተግባራዊ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ መጠን በማደጉ የሀገር ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያሉት፡፡

ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ልዩነቱ ሰፊ ስለሆነ ለኮንትሮባንድና ህገወጥ ግብይት እንዲጋለጥ ከማድረጉም በተጨማሪ በመንግስት ላይ ያለው ጫና በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ በሂደት ከድጎማ ለመውጣት ባለፉት 11 ወራት ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

ይህን ተከትሎም ቤንዚንና የአውሮፕላን ነዳጅ ከግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ፣ ነጭ ናፍጣና ሌሎች የነዳጅ ውጤቶችን ከግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የጥቅል ድጎማውን በማስቀረት በዓለም የነዳጅ ዋጋ መሰረት እንዲሆን መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!