አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶስት የኢራን ኒውክሌር ማዕከላት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሻለሁ አለ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር፡፡
የአሜሪካ ጦር አውሮፕላኖች ኢራን ውስጥ በሚገኙ ሦስት የኒውክሌር ማዕከላት ላይ በዛሬው ዕለት ንጋት ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡
አሜሪካ በእስራኤል እና ኢራን ጦርነት ላይ መሳተፏን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒተር ሄግሴዝ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ÷ አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ማብላያ ማዕከላት ላይ ጥቃት ለመፈጸም አስፈላጊውን ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ዛሬ ንጋት ላይ የአሜሪካ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ላይ የፈጸሙት አስደንጋጭ ጥቃትም ስኬታማ ነበር ብለዋል፡፡
በጥቃቱ ሦስቱም የኢራን ኒውክሌር ማብላያ ጣቢያዎች ከባድ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ጠቅሰው፥በዚህም የማዕከላቱን የኒውክሌር መርሐ ግብር ማውደም ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ጥቃቱን የፈጸሙት ቢ-2 የተሰኙ ቦምብ ጣይ አውሮፕላሎች ዘመኑን የዋጀ ወታደራዊ ቴክኒክ መጠቀማቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ÷በአንጻሩ በኢራን ጦር ምንም አይነት አጸፋዊ ርምጃ እንዳልገጠማቸው አንስተዋል፡፡
አሜሪካ በኢራን የመንግስት ሥርዓት የመቀየር አላማ እንደሌላት ገልጸው÷ይሁን እንጂ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንድትታጠቅ አንፈቀድም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢራን ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በበኩላቸው ÷ አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ላይ የፈጸመችው ጥቃት አደገኛ እና የዲፕሎማሲ መርሕን የጣሰ ነው ሲሉ አውግዘዋል፡፡
ሀገራቸው በአሜሪካ ለደረሰባት ጥቃት አስፈላጊውን አጸፋዊ ርምጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡
ኢራን ሁሉንም አማራጮች ተጠቅማ ሉዓላዊነቷን ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት ትሰራለች ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፡፡
በሌላ በኩል የእስራኤል ጦር ዛሬ በተመረጡ የኢራን ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ በ30 ተዋጊ ጄቶች የተሳካ ጥቃት ፈጽሜያለሁ ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!