የሀገር ውስጥ ዜና

የጤና ተቋማትን ሁለንተናዊ አቅም ለማጠናከር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

June 22, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ተቋማትን ሁለንተናዊ አቅም ለማጠናከር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት እንዳሉት÷ የጤናው ዘርፍ ከሕክምና ባለፈ በዲሲፒሊን የታነጸ ጤናማ ትውልድ ለመገንባት ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡

በዘርፉ የሚነሱ ጥያቄዎችን በፖሊሲ ደረጃ ማየት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ከለውጡ በፊት የነበረው የጤና ፖሊሲ መከላከል ላይ መሰረት ያደረገ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የለውጡ መንግስት ግን መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ በመተግበር በርካታ ለውጦች ማስመዝገቡን አብራርተዋል፡፡

የኮሪደር ልማት እና ሌሎች ንጹሕ አካባቢን ለመፍጠር የሚከናወኑ ሥራዎች ጤናማ ዜጋን ለማፍራት የሚከናወኑ የቀድሞ መከላከል ጤና ፖሊሲ አካል መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

አክሞ ማዳን ፖሊሲ ላይም የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረት መሰራቱን ነው ያስረዱት፡፡

የሕክምና ዘርፉ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር÷ የለውጡ መንግስትም ይህን በተገቢ ሁኔታ ይረዳል ብለዋል፡፡

ለአብነትም ከጥቂት ዓመታት በፊት በቀጥታ ለጤና ሚኒስቴር ፈሰስ የሚደረገው ሃብት 70 ቢሊየን ብር ገደማ እንደነበር ጠቅሰው÷ አሁን ላይ ግን 130 ቢሊየን ብር ገደማ ፈሰስ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ይሄም ለዩኒቨርሲቲዎች እና ለህንጻ ግንባታ የሚመደበውን ገንዘብ እንደማያካትት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ከዚህ አንጻር የትኛውም ጎረቤት ሀገር ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የምትመድበው በጀት እንደማያወጣ እና በዘርፉ የምታከናውነውን መሰረተ ልማት እንደማይገነባም አንስተዋል፡፡

በቀጣይም የጤና ተቋማትን ሁለንተናዊ አቅም ለማጠናከር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ