የሀገር ውስጥ ዜና

ፕሬዚዳንት ታዬ የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እንዲሳተፉ ጠየቁ

By Melaku Gedif

June 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የግብርና ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንቱ በአንጎላ ሉዋንዳ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ አሜሪካ የቢዝነስ ጉባዔ ጎን ለጎን የአፍሪካና የአሜሪካ የግብርና፣ የምግብ እና የቢዝነስ ዘርፍን ለማጠናከር ያለመ የፓናል ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።

በፓናሉ የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቤርት ቡግሬ ማምቤ እና የኤስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ሚሶ ድላሚኒን ጨምሮ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ኩባንያዎች ተወካዮችም ታድመዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በፓናል ውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት÷ አሜሪካ አሁን ላይ በአፍሪካ ያላትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ ያላትን ፍላጎት አድንቀዋል።

አፍሪካ የአሜሪካ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚሆን አቅም እንዳላት ጠቅሰው÷ በአፍሪካ በኩል ሊለማ የሚችል መሬት፣ የሰው ሃብትና ትክክለኛ ፖሊሲ መኖሩን ማረጋገጥ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይም ጠንካራ የምግብ ሥርዓት መዘርጋት፣ አስተማማኝ የንግድ ትስስር መፍጠርና በምርቶች ላይ እሴት የሚጨምር ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ አንጻር የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ለመሳተፍ የሚጋብዝ ከፍተኛ አቅም እንዳለ ጠቁመው÷ ይህም በቅርቡ በተግባር ተፈትኖ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ነው ያሉት።

በተለይም በኢትዮጵያ ለእርሻ ሥራ መዋል የሚችል ሰፊ ለም መሬት እንዳለ እና ይህንን የግብርና ሥራ ሊያከናውን የሚችል የሰው ሃይል መኖሩንም አስረድተዋል፡፡