የሀገር ውስጥ ዜና

ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችል የተፈጥሮ ማዳበሪያን እያመረተ ነው

By Hailemaryam Tegegn

June 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ አፈርን የሚያክምና ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ እየመረትኩ ነው አለ።

ዩኒቨርሲቲው የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችለውንና የማምረት አቅሙ ከፍተኛ የሆነውን ‘ኢሴኒያ ፈቲዳ’ የተባለ ቨርም ዝርያ በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያን በብዛት እያመረተ እንደሆነ ገልጿል፡፡

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፈዬራ ዲንሳ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን ለመተካት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምርቱን ወደ ሕብረተሰቡ ለማዳረስ ከአርሶ አደሩና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ ትምህርት ክፍል ተመራማሪና መምህር ታደሰ ግርማ በበኩላቸው÷ በጥናትና ምርምሮች በመታገዝ የተመረተው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማህበረሰብ አገልግሎት እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተመራማሪው እንደገለጹት፥ በዚህ መልክ የሚዘጋጀው ማዳበሪያ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን በአፈር ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሊቆይ የምችል ነው።

በማዕከሉ የምርምር ስራዎችን በማከናወን፣ በማምረትና በማስተማር ለማህበረሰብ አገልግሎት እያዋልን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮችም በማዕከሉ ሰልጥነው የተፈጥሮ ማዳበሪያውን በራሳቸው ማዘጋጀት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ውጤቱም እያደር የሚታይ እንጂ የሚቋረጥ አለመሆኑን የገለጹት አርሶ አደሮቹ÷ የተፈጥሮ ማዳበሪያው ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ የበለጠ ምርታማ እንደሆነ አይተናል ብለዋል።

በሲፈን መገርሳ