የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ ተጨባጭ አስተዋጽኦ ያላበረከተ ሰው ስልጣን ሊይዝ አይችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

June 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ተግባራት ላይ ምንም አይነት ተጨባጭ አስተዋጽኦ ያላበረከተ ግለሰብ በፍጹም ስልጣን ሊይዝ አይችልም አሉ ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተወጣጡ የሕዝብና የግል ሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ፥ መገናኛ ብዙሃን ለሕዝቡ የሚያቀርቧቸውን ግለሰቦች ማንነትና አስተዋጽኦ መመርመር አለባቸው ብለዋል፡፡

የሚዲያ ሰዎች በትምህርታቸውና በልምዳቸው ብቁ ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመው ፥ ለሕዝብ የሚያቀርቧቸው ግለሰቦች የሰሯቸውን ሥራዎች መጠየቅ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ፣ ችግኝ በመትከልና መሰል የማህበራዊ አገልግሎቶች ተሳትፎ ሳያደርጉ በሚዲያ መጥተው እንደ መልዓክ ለመሆን የሚሞክሩ ሰዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን በሚዲያ ሲያቀርቡ የት እንደሰሩና ለሀገር ያደረጉትን አበርክቶ መጠየቅ ከጋዜጠኞች የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ለሀገር ተጨባጭ አስተዋጽኦ የሌላቸው ግለሰቦች መጥተው ስልጣን መያዝ የሚችሉበት የፖለቲካ ምህዳር እንደሌለ መታወቅ ያለበት ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስት መዋቅር፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም በሚዲያ ውስጥ ሰርገው የገቡ ሰዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

እነዚህ አካላት ይማራሉ በሚል እንዲቆዩ ቢደረግም በሒደት ከእነዚህ ተቋማት ሲወጡ በአንድ ጊዜ የሚጮሁ ከሆነ ችግር መኖሩን ማስተዋል ከሚዲያ ሰዎች ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ