የሀገር ውስጥ ዜና

“የሚዲያ ባለሙያዎች ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር በትኩረት ሊሰሩ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

June 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚዲያ ባለሙያዎች ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር በትኩረት ሊሰሩ ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ እና የግል ሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት እንዳሉት፥ ጋዜጠኛ ትክክለኛ ዓላማ በመያዝ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ሊሰራ ይገባል።

ጋዜጠኝነት የሚቆምለት የራሱ የሆነ ዜግነት፣ ብሔራዊ ጥቅም፣ ሀገር እና ባሕል እንዳለው ጠቅሰው ÷ ይሄን ግምት ውስጥ በማስገባትም ለእውነት በመቆም መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነት ማነስ እና የሰፈር ሚዲያ ብቻ መሆን አሳሳቢ እና ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የሚገኙ የጎረቤት ሀገራት ቋንቋዎችን በመጠቀም ያላቸውን ተደራሽነት በማስፋት ረገድ ውስንነት መኖሩንም አስረድተዋል።

ሚዲያዎች ብዙ ርቀት እንዲሄዱ ከሀገር ውጭ ተጽዕኖ ማሳደር መቻል እንዳለባቸው እና በዘርፉ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል።

የመረጃ ሥርጭትን ለሚዲያ ተደራሽ ለማድረግ በየቀኑ የሚከናወኑ የመንግስት ሥራዎችን ሁሉም አመራር ባለው የማህበራዊ ትሥሥር ገጽ እንደሚያጋራ አንስተዋል።

በሌላ በኩል ተጨማሪ መረጃዎችን የሚጠይቁ እና ምርመራዎችን ማድረግ የሚፈልጉ ጋዜጠኞች ብዙ ዕድል እንደማያገኙ ነው የተናገሩት፡፡

የብሔራዊ ጥቅም ለገባቸው እና በመረጃና በእውነት ላይ ተመስርተው የሚጠይቁ አካላትን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ እንሰራለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡

በዮናስ ጌትነት