አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ አቪዬሽን ድርጅት ቁልፍ የሕዝብ መረጃ ልውውጥ ሥርዓት (ፒኬዲ) አባል መሆኗን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት ተቀብላለች።
ሰርተፍኬቱን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ፕሬዚዳንት እና የካናዳ ትራንስፖርት ም/ሚኒስትር በተገኙበት በካናዳ ተረክበዋል፡፡
ወ/ሮ ሰላማዊት በዚህ ወቅት ÷ ኢትዮጵያ 105 ሀገራትን ባቀፈው ፒኬዲ አባል መሆኗ የሀገርን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ በሆነው የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ትብብር ሥርዓት ውስጥ የላቀ ቴክኖሎጂን መጠቀሟ ድንበሯን ከመጠበቅ ባለፈ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የጋራ ደህንነት መጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት፡፡
ኒኮላስ ሮብሰን በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ ወደ ሥርዓቱ በይፋ መቀላቀሏ በአቪዬሽን ዘርፍ የምታከናውነው ሥራ በዓለም የታመነ እንዲሆን ያስችላልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የማዕቀፉ አባል መሆኗ የኢትዮጵያን ፓስፖርት የያዙ ዜጎች በአባል ሀገራቱ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ያለምንም እንግልት እንዲጓጓዙ ያስችላል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ በየብስም ሆነ በአየር በተጭበረበረ የጉዞ ሰነድ ለመምጣት የሚሞክሩ አካላትን በቀላሉ ለመለየት እንደሚረዳ ነው የተመላከተው፡፡
በሀገር ላይ ሊቃጣ የሚችል የደህንነት ስጋትን አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚያግዝም የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ማስተዋል ገዳ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡