አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መገናኛ ብዙኃን በሚሰሯቸው ይዘቶች ለውጦችን ሊረዱ ይገባል አሉ የአፍሪካ አመራር ልሕቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ፡፡
አቶ ዛዲግ አብርሃ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አመራሮች እና ባለሙያዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና እየሰጡ ነው፡፡
በዚህ ወቅትም የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎች በጊዜ እና በብሔራዊ ጥቅም ዓውድ መበየን እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
ዓለም የማያቋርጡ ግጭቶች፣ ቀውሶችና ሌሎች ተለዋዋጭ ጉዳዮችን እያስተናገደች ነው ያሉት አቶ ዛዲግ ÷ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ትርክትን በዓውድ መመስረት ይገባል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከይዘት በፊት ዓውድን መሰረት ያደረገ የተግባር እቅድ መገናኛ ብዙኃን መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ዓውድ ተቀያያሪ በመሆኑ መገናኛ ብዙኃንም ሁኔታውን በመረዳት ይዘቶችን ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ