አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ መድንን ሻምፒዮን በማድረግ ከሊጉ ከሚሰናበቱ አራት ክለቦች መካከል 3ቱን ከወዲሁ ወደ ከፍተኛ ሊግ ሸኝቶ የውድድር አመቱን ሊቋጭ ሦስት ጨዋታዎች ብቻ ቀርተውታል፡፡
አዳማ ከተማ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ተከትሎ ከፕሪሚየር ሊጉ የሚወርደውን ክለብ የሚወስነው የ90 ደቂቃ ፍልሚያ በዛሬው ዕለት ይደረጋል፡፡
ምሽት 12 ሰዓት በሚደረገው የሊጉ የመጨረሻ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መቐለ 70 እንደርታ ከባድ ትንቅንቅ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታውን ከማከናወኑ አስቀድሞ በሊጉ የመቆየት ዕድል የነበረው አዳማ ከተማ ትናንት በሀዋሳ ከተማ ተሸንፎ ከፕሪሚየር ሊጉ ለመውረድ ተገዷል፡፡
በ41 ነጥብ በ2 የግብ ዕዳ በሊጉ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በተመሳሳይ ነጥብ በ8 የግብ ዕዳ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ የዛሬ ተፋላሚዎች ናቸው፡፡
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከዛሬው ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘት ከቻለ ከተጋጣሚው መቐለ 70 እንደርታ በግብ ክፍያ በመብለጥ በፕሪሚየር ሊጉ መቆየቱን ያረጋግጣል፡፡
መቐለ 70 እንደርታ በአንጻሩ ከሊጉ ላለመውረድ ማሸነፍን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉትን የሊጉ ጨዋታ ጨምሮ ባለፉት ሦስት ግንኙነታቸው መቐለ 70 እንደርታ 3ቱንም በማሸነፍ የበላይነት አለው፡፡
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች 2ቱን አሸንፎ በሁለቱ አቻ ሲለያይ፥ በቀሪው አንድ ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡
መቐለ 70 እንደርታ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች 3ቱን በማሸነፍ በሁለቱ አቻ የተለያየ ሲሆን፥ ምንም ሽንፈት አላስተናገደም፡፡
በ35ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፍ የቻሉት ሁለቱም ክለቦች ዛሬ የ2018 የውድድር ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ መሆናቸውን በራሳቸው የሚያረጋግጡበትን ተጠባቂ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡
በሌላ የሊጉ የመጨረሻ ሳምንት መርሐ ግብር፥ ባህር ዳር ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቀን 9 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ባህር ዳር ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ የውድድር አመቱን 3ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቅቃል፡፡
የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመዝጊያ መርሐ ግብር ነገ የሚከናወን ሲሆን፥ ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ መድን ከሊጉ አስቀድሞ የወረደውን ስሑል ሽረ ይገጥማል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ