አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ7 ቢሊየን ብር ወጪ ግንባታው እየተጠናቀቀ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ መንደር ለአገልግሎት ለማብቃት በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ፡፡
ከንቲባ አዳነች በአዲስ አበባ ከተማ በ7 ቢሊየን ብር ወጪ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ መንደር ጎብኝተዋል፡፡
በዚህ ወቅትም የነዋሪዎችን ጥያቄ የምንመልሰው የሚታዩ ፣ የሚጨበጡ እና ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ በማተኮር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
93 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የኢንዱስትሪ መንደሩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ከ120 በላይ ሼዶች እንዳሉት አስረድተዋል፡፡
ሼዶቹ ለብረታብረት ሥራ፣ ለእንጨት ውጤቶች፣ ለጨርቃ ጨርቅ፣ ለፕላስቲክ እና ለኬሚካል ማምረቻነት፣ የምርት ማሳያ እና መሸጫ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ናቸው።
የኢንዱስትሪ መንደሩ ግንባታ የመስሪያ ቦታ ችግርን ከማቃለል ባሻገር የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ሰፊ የሥራ ዕድልን ለመፍጠርና የኢኮኖሚ ሽግግርን በማሳለጥ ረገድ ሚናው ጉልህ ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ የግንባታው 2ኛ ምዕራፍ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች የሚሆኑ ሼዶችን የያዘ ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ መንደሩ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሼዶች በተለየ ሁኔታ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግብዓቶችን እንዲጠቀም ተደርጎ እየተገነባ ነው።
ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በጥቂት ደቂቃ መድረስ የሚያስችል አዲሱ የአቃቂ ቦሌ ካርጎ መንገድ ላይ እና ምርት ማጓጓዝን ታሳቢ ያደረገና ስትራቴጂክ ስፍራ ላይ እንደሚገኝም የከንቲባ ጽ/ቤት ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!