ስፓርት

የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተጠናቀቀ

By Yonas Getnet

June 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2017 የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ መድን አሸናፊነት ተጠናቅቋል።

ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት በተካሄደው የውድድር ዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን እና ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ስሑል ሽረ ባደረጉት ጨዋታ ፍጻሜውን አግኝቷል።

በጨዋታው የሊጉ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ መድን በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራቸው 3 ግቦች ስሑል ሽረን 3 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

የመድንን ማሸነፊያ ግቦች አቡበከር ሳኒ፣ ወገኔ ገዛኸኝ እና ዋንጫ ቱት አስቆጥረዋል፡፡

በሌላ በኩል የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቹ ዓሊ ሱለይማን በ21 ግብ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የውድድር ዓመቱን አጠናቅቋል።

እንዲሁም የውድድር ዓመቱ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ መድንን በአሰልጣኝነት የመሩት ገብረመድህን ኃይሌ የዓመቱ ኮኮብ አሰልጣኝ በመባል የተመረጠ ሲሆን÷ ይህንን ሲያሸንፍ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ተገልጿል።

ከተለያዩ ሦስት የፕሪሚየር ሊጉ ቡድኖች ጋር በመሆን የሊጉን ዋንጫ በማሸነፍ የመጀመሪያው የሆኑት አሰልጣኝ ገብረመድህን የ200 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።

በውድድር ዓመቱ የኢትዮጵያ መድኑ አምበል ሀይደር ሸረፋ የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠ ሲሆን÷ ከሦስት የተለያዩ ክለቦች ጋር ዋንጫ ያነሳ በታሪክ 2ኛው ተጫዋች ነው።

በሰለሞን በቀለ