የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የቱሪዝም ልማቱን በማነቃቃት ኢኮኖሚያዊ አበርክቶውን ለማጉላት እየተሰራ ነው

By Adimasu Aragawu

June 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት የሚኖረውን አበርክቶ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በቱሪዝም እንቅስቃሴ፣ በቅርስ ጥበቃና ፓርኮች ልማት ዙሪያ የምክክር መድረክ ዛሬ በባህር ዳር አካሄዷል።

አቶ አረጋ ከበደ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት እንዳሉት÷ በክልሉ በተለያዩ ችግሮች የተጎዳውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ከሚኒስቴሩ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።

የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ በመምጣቱ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና የለሙትን በማስተዋወቅ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ እንደ አንኮበር፣ ይስማ ንጉስ፣ ውጫሌና ሌሎች የመዳረሻ ቦታዎችን በማልማት የቱሪዝም ልማቱን ለማሳደግና የቱሪስት የቆይታ ጊዜን ለማራዘም እየተሰራ ነው ብለዋል።

የቱሪዝም ሃብቱን ለማሳደግ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው÷ ሚኒስቴሩ በክልሉ ያሉ ዕምቅ የቱሪዝም ሃብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችን ለመሳብ በጋራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና ነባር ቅርሶችን በመጠገን የክልሉን ህዝብ ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ክልሉ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በርካታ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተገንዝበናል ያሉት ሚኒስትሯ÷ ቱሪዝም ሰላምን አጥብቆ የሚሻ መሆኑን በመገንዘብ መስራት ይገባል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!