የሀገር ውስጥ ዜና

“ማሻሻያው በሁሉም አመልካቾች የሚጠበቅበትን ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል” አቶ ማሞ ምህረቱ

By Yonas Getnet

June 27, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁሉም አመልካቾች የሚጠበቅበትን ውጤቶች እያስመዘገበ ነው አሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዠ ማሞ ምህረቱ፡፡

አቶ ማሞ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ÷ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ በሚያስችል አበረታች ሒደት ማስመዝገቡን አንስተዋል፡፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተያዘለት የገቢ ማሳደግ፣ የዕዳ ሽግሽግ፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚን ማምጣት፣ የውጪ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ ብሎም የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማ ከማድረግ እንዲሁም ሌሎች ዓላማዎቹን ከማሳካት አኳያ አመርቂ ውጤቶች ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸሙ በውጤታማነት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ በወጪ ንግድ፣ በውጪ ምንዛሪ ክምችት፣ የዋጋ ንረትን በመቀነስ እንዲሁም በሌሎችም አመርቂ ውጤቶች እየታየበት ነው ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙን ከሚደግፉት መካካል ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም አፈጻጸም ከታቀደለት ግብ በላይ በማሳካት ላይ መሆኑን ማረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የዋጋ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ነው ያስረዱት፡፡

የምግብ ነክ የዋጋ ንረት ከ12 በመቶ በታች መሆኑን ያነሱት የባንኩ ገዥ÷ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ለማሳካት ጥብቅ የሆነ የገንዝብና የፊሲካል ፖሊሲ እንደሚወሰድ አመልክተው ÷ ምርታማነትን ማሳደግ፣ እሴት በመጨመር የንግድ ሥርዓቱን ማሳለጥ እና ሌሎች ርምጃዎች እንደሚወሰዱ ጠቁመዋል፡፡

በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ውስጥ የተወሰደው ርምጃ ሥር ነቀልና ተመኑን በገበያ ከመወሰን ባለፈ በአጠቃላይ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓቱ የተሻለ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በማምጣት ላይ የሚገኘው ውጭ ምንዛሪ ፍሰት መጨመሩን አንስተው ጠቅሰው÷ ባለፉት 11 ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ማደጉን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ሪፎርሙ በፊት የሀገሪቷ የወጪ ንግድ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር እንደነበር አስታውሰው÷ አሁን ላይ ይህ ዓመት በሚጠናቀቅበት ጊዜ የወጪ ንግድ8 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ ጠቁመዋል፡፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የታቀደለትን ግቦች በማሳካት ላይ የሚገኘው በቂ ዝግጅትና ጥናቶች ተደርገው ወደ ስራ በመግባቱ መሆኑን ገልጸው÷ ሪፎርሙ በርካታ ጉዳዮችን አሰባስቦ መተግበሩ ለውጤታማነት ማብቃቱን ተናግረዋል፡፡

ማሻሻያው ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ረገድ ትልቅ ውጤት እያስገኘ ነው ያሉት አቶ ማሞ÷ በቀጣይም የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡