የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሁሉም አረዓያ የሚሆን ነው – የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት

By Abiy Getahun

June 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት ለሁሉም ሀገራት አረዓያ የሚሆን ነው አሉ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ውጥን እንዲሳካ በማድረግ ረገድ የዘመናዊ አመራር ተምሳሌት መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ የአየር ንብረትን ለውጥ ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ በሚያበረክተው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያስመዘገበች ያለውን ለውጥ አድንቀዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አደጋ የደቀነ እና ተግባራዊ እርምጃ የሚያስፈልገው የጋራ ጉዳያችን ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ለችግሩ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት አብነት የሚሆን ስራ ማከናወኗን ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ራዕይና ቁርጠኝነት ያሳያል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የያዙ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የጋራ ህልም ይዘው ለአፍሪካ የተሻለ እጣ ፋንታ መስራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ከሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች መሆኑ ደግሞ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ውጥን እንዲሳካ በማድረግ ረገድ የዘመናዊ አመራር ተምሳሌት መሆናቸውንም አንስተዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!