አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ፅዱ አካባቢን ለመፍጠር ሁሉም አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ተጠየቀ።
ፅዱ ሀረርን ባህል ማድረግ በሚል መሪ ሃሳብ ሁለተኛው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ህዝባዊ ንቅናቄ ተጀመረ።
የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ (ኢ/ር) በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአካባቢ ብክለት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና ለተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መንስኤ እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።
በተለይም የፕላስቲክ ምርቶችን አብዝቶ መጠቀም ለአካባቢ ብክለትና ለፅዳት መጓደል መንስኤ በመሆኑ የፕላስቲክ አጠቃቀም ላይ ገደብ በማበጀት ከቆሻሻ የፀዳ አካባቢን ለልጆቻችን ማውረስ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ነቢላ መሃዲ በበኩላቸው፥ የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የፅዳት፣ የውበትና የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ቀጣይነት ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የሀረር ከተማን በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ከፕላስቲክ ብክለት የፀዳች ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን ስርዓት ለማስያዝ እንዲሁም የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል የማድረግ ህዝባዊ ንቅናቄ በአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም በድምፅ ብክለትና የቆሻሻ አስተዳደርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ለስድስት ወራት ይካሄዳል፡፡
የህዝባዊ ንቅናቄ መድረኩ ተሳታፊዎች የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላን አካሂደዋል።
በተሾመ ኃይሉ