አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መገናኛ ብዙሃን ሙስናን ለመታገል ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል አሉ የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፡፡
የኦሮሚያ ክልል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሚዲያ ለስነ ምግባር ግንባታ እና መልካም አሰትዳደር በሚል መሪ ሃሳብ ለመገናኛ ብዙሃን እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ ሙስና ለሀገር እድገትና ልማት እንቅፋት በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን ሙስናን ለመታገል ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ እውነትን መግለጥና ስነ ምግባር ያለው እንዲሁም መብትና ግዴታውን የሚያውቅ ዜጋ መፍጠር ከመገናኛ ብዙሃን እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት፡፡
ከጎሳ፣ ሃይማኖትና ብሄር አስተሳሰብ በመውጣትና አድሏዊ አሰራርን በመተው ሁሉንም ዜጋ እኩል ማገልገል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽነር አብደላ ኦጋቴ በበኩላቸው፥ የሙስና ወንጀልን በመከላለከል ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ስርቆት ባለበት ፍትህ፣ ሰላም፣ አንድነት፣ ባህል እና እሴት እንደማይኖርም ተናግረዋል፡፡
በአቤል ንዋይ