የሀገር ውስጥ ዜና

ተማሪዎች ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለ አበርክቶ እንዲኖራቸው በርትተው መስራት አለባቸው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

By Adimasu Aragawu

June 30, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ተማሪዎች ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለ አበርክቶ እንዲኖራቸው ፈተናውን በርትተው መስራት አለባቸው አሉ።

ሚኒስትሩ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ጋር በመሆን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተናን በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አስጀምረዋል፡፡

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ ተማሪዎች ራሳቸውን በእውቀት አዳብረው ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለ አበርክቶ እንዲኖራቸው ለማድረግ ፈተናውን በርትተው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

ለተፈተኞች መልካም ውጤትን በመመኘት ተማሪዎች ሙሉ ትኩረታቸውን በፈተናው ላይ እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ተማሪዎችን ለፈተናው በተዘጋጁት ልክ ተረጋግተው እንዲሰሩና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው በማሳሰብ ለተማሪዎች መልካም ውጤት ተመኝተዋልም ነው ያሉት።

በክልሉ 19 ሺህ 127 ተማሪዎች በፈተናው ላይ እንደሚቀመጡና ከነዚህም ውስጥ 9 ሺህ 758 የማህበራዊ ሳይንስ እንዲሁም ቀሪዎቹ 9 ሺህ 369 ተማሪዎች የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መሆናቸው አብራርተዋል።

በዛሬው ዕለት በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ዞኖች ወደ ፈተና ማዕከላት የተመደቡ የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናቸውን እየወሰዱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም በወረቀትና በኦላይን እንደሚሰጥ የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ማሳወቁ ይታወሳል።

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!