ቢዝነስ

815 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

By Melaku Gedif

June 30, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 815 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገቢዎች ሚኒስቴርን 11 ወራት አፈጻጸም ገምግሟል።

የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት ÷ በበጀት ዓመቱ ከሀገር ውስጥ ታክስና ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ ከ900 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

እስካሁን ባሉት የበጀት ዓመቱ 11 ወራት 815 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ነው ያብራሩት።

በወጪና ገቢ ኮንትሮባንድ ላይ በተደረገው የቁጥጥር ስራ 19 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ጠቅሰው ÷ የተለያዩ ዲጂታል የቴክኖሎጂ አሰራሮችን በማልማት ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል፡፡

የሥነ ምግባር ጉድለት የታየባቸው 405 ሰራተኞች ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ስንብት የሚደርስ ርምጃ ከመውሰድ ባለፈ በወንጀል እንዲጠየቁ መደረጉን አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ ቀጣይነት ያለውና የሀገር ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋልም ነው ያሉት፡፡

በደረሰኝ የሚስተዋሉ ማጭበርበሮችን ለመከታተል እንዲያመች በኪውአር ኮድ የተደገፈ ደረሰኝ ወደስራ ለማስገባት ከአሳታሚ ድርጅት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

700 ሺህ የእጅ በእጅ ሽያጭ ደረሰኝ ህትመት ለማድረግ ታስቦ ወደ ስራ ቢገባም ፍላጎቱ በሶስት እጥፍ ያደገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ መሰረት የአሳታሚውን ድርጅት አቅም የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ከመሆኑ ባለፈ ወደ ዲጂታል የደረሰኝ አገልግሎት ለመግባት እየተሰራ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አዝዘው ጫኔ በበኩላቸው÷ ሕገወጥ ኬላዎች በወጭና ገቢ ንግድ ሥርዓቱ እንዲሁም በሀገራዊ ገቢ ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማስቀረት የሚደረገው ሕግ የማስከበር ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!