አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በ10ኛው የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ እንዲሁም ለወደፊት ያለመቻቸውን የልማት ግቦች አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበች እንደምትገኝና በርካታ ሪፎርሞችን እንዳከናወነች አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተግባራዊ ካደረገቻቸው ሪፎርሞች አንዱ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሆኑን ጠቁመው ÷ማሻሻያው ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲሁም የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ኢኒሼቲቮችን ተግበራዊ በማድረግ በአየር ንብረት ለውጥ እና አካባቢጥበቃ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን ነው ያስረዱት፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች የውስጥ መፍትሔ እያፈላለገች እንደምትገኝ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አቶ አሕመድ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከተሰናባቹ የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር መምከራቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡