አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ብዝሃነትን ማስተናገድና ሕብረብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር አለብን አሉ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝቦች የሠላም፣ የአንድነት እና የልማት ኮንፈረንስ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት አቶ አደም ፋራህ፤ የሀገራችን ብዝሃነት ውበት ማሳያ የሆነው ክልሉ በሕዝቦች ተሳትፎ በሕገመንግሥታዊ መንገድ በጥንቃቄ መመራቱ በፍጥነት ሥራ እንዲጀመር አስችሏል ነው ያሉት።
በክልሉ ያሉት የታሪክ፣ የባህልና የተፈጥሮ እምቅ ፀጋዎች ክልሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የብልጽግና ተምሳሌት እንዲሆን ያስችለዋል በማለት ገልጸው፤ ለም መሬቱ፣ የተፈጥሮ ሀብቱ እና ታታሪ ሕዝቦቹ የልማት ምሰሶ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ያለውን አቅም ለመጠቀም የተደረገው ጥረት ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰው፤ በፖለቲካ መስክ የክልሉን ተቋማት አደራጅቶ ወደ ሥራ በማስገባት፣ የሕዝብ ንቅናቄ እና የአመራር አንድነት የሚያመጡ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
የግብርና ምርታማነት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ገቢ ማሳደግ ላይ በኢኮኖሚ መስክ በክልሉ የተሰሩ ስኬታማ ሥራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሠረተ ልማት ረገድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ኮሪደር ልማትና መንገድ ተሰርቷል በማለት ገልጸው፤ ይሁንና ክልሉ ያለውን እምቅ አቅም በሚፈለገው ደረጃ ተጠቅሟል ማለት እንደማይቻል ጠቁመዋል።
ለዚህም የተቋማት አለመጠናከር፣ የልሂቃን ክፍፍልና ያልተገባ እንቅስቃሴ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል አለመተማመንን የሚያስከትሉ ነጠላ ትርክቶች የክልሉን ዕድገት በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል።
እነዚህን ክፍተቶች መነሻ በማድረግ በባለድርሻ አካላት መካከል መግባባት ለመፍጠር መድረኮች መዘጋጀታቸውን አድንቀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 32 ብሔሮችን አቅፎ በመያዝ በብዝነት ቀዳሚ ክልል ነው ያሉት አቶ አደም ፋራህ፤ በመደመር ፍልስፍና ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ሕብረብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድም እንደሚገባ አስረድተዋል።
በመለሰ ታደለ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!