የሀገር ውስጥ ዜና

በሚቀጥለው በጀት ዓመት ክልሎች ንብረት ታክስን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ይጀምራሉ

By abel neway

July 01, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ክልሎች የንብረት ታክስን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ይጀምራሉ አሉ።

አቶ አህመድ ሺዴ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 41ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በፌዴራል መንግስት የ2018 ረቂቅ በጀት ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ እዳ እየከፈለ የሚገኘው መንግስት በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ገቢ እያገኘ መምጣቱን ገልጸው፤ ገቢ የማያስገኝ አገልግሎት አክሳሪ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ የንብረት ታክስ ክፍያ ተግባራዊ መደረጉን በማስታወስ፤ በሚቀጥለው በጀት ዓመት የንብረት ታክስ በክልሎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ይጀመራል ነው ያሉት።

አዲስ መንገዶችን ለመስራት በበቂ ሁኔታ ጥናት ማደረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ አህመድ፤ ባለፉት 7 አመታት የልማት ኢ-ፍትሐዊነት ከተነሱባቸው መካከል መንገድ ዋነኛው መሆኑን ነው ያነሱት።

የመንገድ ፕሮጀክቶች እቅድ እና የተያዘላቸው በጀት ተመጋጋቢ እንዳልነበሩ ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመፍታት በቂ ጥናት ተደርጎ ወደ ትግበራ ይገባል ብለዋል፡፡

ለመንገድ የተመደበው በጀት ከሁሉም ሴክተሮች እንደሚበልጥም ነው ያነሱት አቶ አህመድ ሺዴ፡፡

የመልሶ ማቋቋምን በተመለከተም መንግስት በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡

የካሳ ክፍያ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና እያስከተለ በመሆኑ ለካሳ ክፍያ በሚል የሚደረጉ ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች ላይ ክልሎች በትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡

በዚህም የመሰረተ ልማት አስፈላጊነት ላይ ህዝቡ ግንዛቤ እንዲጨብት በማድረግ መንግስት ያለበትን የወጪ ጫና መቀነስ ያስፈልጋል ነው ያሉት ፡፡

በጀቱ ድህነትን ለመቅረፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው እና የማክሮ ኢኮኖሚውን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝም አስገንዝበዋል።

በአቤል ንዋይ