አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 በጀት ዓመት ከ6 ሺህ በላይ ምርመራዎችን በማከናወን ከ5 ሺህ 600 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል አለ የፌደራል ፖሊስ፡፡
የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ እና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ተወካይ ሙሊሳ አብዲሳ በሰጡት መግለጫ÷ ቢሮው በሽብር ወንጀል፣ ታክስ ማጭበርበር እና መሰል ወንጀሎች ላይ ምርመራዎችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል፡፡
ከተቋማት እና ሕብረተሰቡ ጋር በተሰራው ሥራ ህብረተሰቡን የሚያወናብዱ ሀሰተኛ መረጃዎችን ባጠረ ጊዜ በማጋለጥ ተሳታፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ማድረግን ጨምሮ ከውስጥና ከውጭ በተደራጁ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም የሞከሩ ከ450 በላይ ተጠርጣሪዎች ወደ ህግ ማቅረቡን አብራርተዋል፡፡
በሞባይል ባንኪንግ ወንጀል ዋና ተዋናዮች ከ80 በላይ ተጠርጣሪዎችን፣ በሙስና ወንጀል 260፣ በህገወጥ መሳሪያ ዝውውርና ሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ላይ የተሰማሩ 143 ተጠርጣሪዎችን፣ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር የተሳተፉ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 86 ተጠርጣሪዎችን እና 25 በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል ምንጫቸው ባልታወቁ የኦንላይን ግብይቶች፣ የሞባይል ባንኪንግና የተለያዩ የኦን ላይን አገልግሎቶች መፈፀሙን የተናገሩት ኃላፊው÷ ማህበረሰቡ ከመሰል መጭበርበሮች ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።
የፎረንሲክ ምርመራ ስራን ለማሳደግ በተሰራው ስራ የዲኤንኤ ምርመራ፣ የእሳት ቃጠሎ እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመመርመር በፍጥነት መለየት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ከ6 ሺህ በላይ ምርመራዎችን በማከናወን ከ5 ሺህ 600 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ያስታወቀው የፌደራል ፖሊስ÷ 1 ሺህ የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓልም ብሏል።
በአጠቃላይ 104 ቢሊየን ብር የሚገመት ጉዳት የደረሰባቸውን የምርመራ መዝገቦች ባማከለ መልኩ ለመስራት ተችሏል ነው ያለው።
ማህበረሰቡ ወንጀልን ለመከላከል በሚሰራው ዘርፈ ብዙ ተግባር ተሳትፎና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
በቅድስት አባተ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!