አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በዘንድሮው ክረምት ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።
በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ÷ ለ2017 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው 1 ነጥብ 55 ቢሊየን ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መደረጋቸውን ነው ለፋና ዲጂታል የተናገሩት፡፡
ከተዘጋጁ ችግኞች ውስጥ ፍራፍሬ፣ ሀገር በቀል የደን ችግኞች፣ የእንስሳት መኖ እና ሌሎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
ለመርሐ ግብሩ በቂ የመትከያ ቦታ መዘጋጀቱን ጠቁመው÷ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ጉድጓድ መቆፈሩን አንስተዋል፡፡
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የችግኝ ተከላ መጀመሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ÷ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ቀናት ክልል አቀፍ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡
ከመርሐ ግብሩ ጋር በተያያዘ ለመትከያ ቦታዎች የካርታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የማዘጋጀት ሥራ መጠናቀቁንም አስረድተዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ እንደወትሮው በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በንቃት እንዲሳተፍም አቶ እስመለዓለም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!