የሀገር ውስጥ ዜና

ለ15 ዓመታት ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ የቆየው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት…

By Hailemaryam Tegegn

July 02, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ቦሬቻ ወረዳ ስራው ተጠናቅቆ ለ15 ዓመታት ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ የቆየውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በተመለከተ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት ለረዥም ጊዜ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎቹ፥ ጥያቄያቸው ምላሽ አግኝቶ የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋቱን ያስታውሳሉ፡፡

በ2002 ዓ.ም የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ተከናውኖ በየቤታችን እንዲገባ አስፈላጊውን ሁሉ አድርገን ብንጠብቅም መሰረተ ልማቱ ሲወድም ብቻ ነው እየተመለከትን ያለነው ሲሉ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

ከብዙ ዓመታት ጥበቃ በኋላ በ2013 ዓ.ም የወዳደቀው የኤሌክትሪክ ምሰሶ እና የተራገፈው ገመድ ተነስቶ ለመጠገን ዳግም ሙከራ ተደርጎ እንደነበር ነው ነዋሪዎቹ የሚገልጹት፡፡

ነገር ግን ትራንስፎርመር ሊያነሱ ሲሉ ተቀያሪ ሳታመጡ ለምን ታነሳላችሁ ብለን ከልክለናል የሚሉት ነዋሪዎቹ፥ ሆኖም ተቀያሪው ትራንስፎርመር ሳይመጣ የተጀመረውም ሳይጠናቀቅ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል በማለት አስረድተዋል።

የተመለሰልን የዘመናት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥያቄ ለ15 ዓመታት ኑሯችንን ሳያቀልልን መቅረቱና ለብልሽት የተዳረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓቶች መመልከት እንደ ማህበረሰብ ያማል ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የወረዳውን ነዋሪዎች ጥያቄ ተቀብሎ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የመቱ ሪጅን ዳይሬክተር ለሆኑት አቶ ዳበላ ፍቃዱ አቅርቧል፡፡

በነዋሪዎቹ የተነሳውን ችግር ለማስተካከል ዳግም ወደ ወረዳው ስንገባ ከማህበረሰቡ የተወሰኑ ግለሰቦች ጋር መስማማት አለመቻላችን መፍትሄ እንዳንሰጥ አድርጎናል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አብዛኛው ንብረት መበላሸቱን እኛም ተመልክተናል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ ችግሩ መቼ እንደሚፈታ ባይገልጹም ዳግም በመልሶ ማልማት እቅድ መያዝ መፍትሄ ይሆናል ሲሉ ነግረውናል፡፡

ለወረዳው ነዋሪዎች ቅሬታ ምላሽ ለማሰጠት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኦሮሚያ ሪጅን ማስተባበሪያ ቢሮ ምክትል ስራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ ግርማ ወልቀባን ጠይቀናል፡፡

አቶ ግርማ በሰጡን ምላሽ፥ የችግሩ ምንጭ የቴክኒክና የመሰረተ ልማት ግብዓት ስርቆት መሆኑን ገልጸው፥ ለወረዳው የሚያስፈልገው 15 ኪሎ ቮልት ትርንስፎርምር ቢሆንም፥ በስህተት 30 ኪሎ ቮልት ትርንስፎርመር መተከሉ ዋነኛው የችግሩ መንስኤ ነው ብለዋል፡፡

የቴክኒክ ችግሩን ለመፍታት በቅድሚያ ከማህበረሰቡ ጋር መግባባት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፥ ትራንስፎርመሩ መቀየር እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት፡፡

በቀጣይ ለሥራው በጀት ለመያዝ አስቀድሞ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ማህበረሰቡን የማግባባት ሥራ እንሰራለን ብለዋል።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነዋሪዎቹ ላቀረቡት ጥያቄ የሚመለከታቸው አካላት በሰጡት ምላሽ መሰረት ጉዳዩ ከምን እንደደረሰ እየተከታታለ እንደሚያቀርብ ለመግለጽ ይወዳል፡፡

በማርታ ጌታቸው