የሀገር ውስጥ ዜና

ዘንድሮ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቁ ድሎች የተመዘገቡበት ዓመት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Adimasu Aragawu

July 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዘንድሮ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ዘመን ነው በሚል በጀመርነው ሥራ ታላላቅ ድሎች የተመዘገቡበት፣ አመርቂ ውጤቶች የታዩበት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቁ ድሎች የተመዘገቡበት ዓመት ነው አሉ።

ለተገኘው ድልም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነበረው አስተዋጽዖ አመስግነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ሪፎርሙን የጀመርነው ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውን፣ ማኅበራዊ ዘርፍን እንዲሁም ተቋማትን የነበረውን ሳናፈርስ በጎደለው ላይ እየሞላን መለወጥ ይቻላል በሚል ዕሳቤ ተሰርቷል ብለዋል።

ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ ያስገቡ ጉዳዮችን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የማክሮ ኢኮኖሚክ ስብራቶችን ለመጠገን፣ የግሉ ዘርፍ መነቃቃት እንድችል የሥራ ከባቢውን ምቹ ለማድረግ፣ ምርታማነትን በግብርናውና በኢንዱስትሪው ያለውን ውስንነት፣ ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ለመፍጠር በማለም ወደ ማሻሻያው መገባቱን ተናግረዋል።

የዓለም የንግድ ሥርዓት በዋዠቀበት ሁኔታ እኛ በምን ዓይነት ስልት ያቀድነውን ልናሳካ እንችላለን የሚለውን ማየት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ወደ አፍሪካ የሚፈሰው እርዳታ 7 በመቶ መቀነሱንና ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁመዋል።

በዚህም ሪፎርሙ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ከውጭ ባለን ትስስር የምናገኘውንና የምናጣውን በማሰብ በሀገር ውስጥ ያለውን እምቅ አቅም በመመንዘር ልናገኝ የምንችለው ውጤቶች በለካ መንገድ የተቀመጠ ነው ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅንጅትና ትብብር እንዲሁም በምክር ቤቱ ቀጥተኛ አመራር የ8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት መረጋገጡን አስታውሰው÷ በዚህ ዓመትም 8 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል።

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook WMCC TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!