አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዘንድሮ በጀት ዓመት 900 ቢሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ነው።
በዚሁም በዘንድሮ በጀት ዓመት 900 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን አንስተው÷ አጠቃላይ ወጪው ደግሞ 1 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር እንደሆነና የ300 ሚሊየን ብር ልዩነት እንዳለው አመላክተዋል።
ገቢው ከአጠቃላይ ጥቅል ምርት አንጻር በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው÷ 46 ሺህ የሚጠጉ የታክስ ተመዝጋቢዎች ግብር እየከፈሉ አለመሆናቸውንም አብራርተዋል።
ከታክስ ተመዝጋቢዎቹ መካከል ከፊሉ የኪሳራ ሪፖርት በማቅረብ፣ ከፊሉ ገቢና ወጪው ተመጣጣኝ ነው፤ ትርፍ የለኝም በማለት ከፊሉ ደግሞ ሪፖርት የማያቀርብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ደ/ር)÷ ኢትዮጵያ ውስጥ ንግድ ፈቃድ ከወሰዱት መካከል ግብር እየከፈሉ ያሉት 37 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ብለዋል።
ከእነዚህም የሚሰበሰበው ገቢ ከአጠቃላዩ 60 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን እንደሆነና 40 በመቶው ገቢ ከተለያዩ ምንጮች እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በመሆኑም ዘንድሮ 37 በመቶ ብቻ የሆነውን የግብር ከፋይ ቁጥር 50 በመቶ ማድረስ ከተቻለ ከታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ይጨምራልም ነው ያሉት።
የታክስ አስተዳደር ችግርን ለማስተካከል ሪፎርም እየተደረገ እንደሆነና ግብር ስወራን ማስቀረት እንደሚያስፈልግ ገልጸው÷ ኢ-መደበኛ የደረሰኝ ጉዳዮችን ማስተካከል ያስፈልጋልም ብለዋል።
ግብር አከፋፈልን ዲጅታላይዝ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትም ውጤት እያመጡ መሆናቸውን አመልክተው÷ ግብር ከፋዮች በታማኝነት ግብር መክፈል ካልቻሉ መንገድ፣ ውሃ፣ ትምህርት በጥቅሉ ሀገር የለም ማለት ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
ይህን ታሳቢ በማድረግ የንግዱ ማህበረሰብ ግብር በታማኝነት ሊከፍሉ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
በአድማሱ አራጋው
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!