የሀገር ውስጥ ዜና

ሕዳሴ ግድብን እንዳይመረቅ የሚያስችል ነገር አሁን የለም- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

July 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እንዳይመረቅ የሚያስችል ነገር አሁን የለም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከም/ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡

በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እንዳይመረቅ የሚያስችል ነገር አሁን የለም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አልቋል፣ ግድቡን እናስመርቃለን፣ ከመመረቁ በፊት ብንረብሽ ብለው የሚያስቡ ሰዎች ይኖራሉ፣ አሁን ግን ሕዳሴ ግድብ እንዳይመረቅ የሚያስችል ነገር የለም ነው ያሉት፡፡

የሚመረቀውም ክረምቱ ሲያልቅ መስከረም ወር ላይ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡

ሕዳሴ ለግብጽም ሆነ ለሱዳን በረከት ነውበፍጹም ጉዳት አያመጣባቸውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ለአብነትም በግብፅ አስዋን ግድብ አንድ ሊትር ውሃ አልቀነሰም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እስከበለጸገችና እስካደገች ድረስ የግብፅ እና የሱዳን ወንድሞቻችንን ጉዳት አንፈልግም ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ለመነጋገር፣ ለመደራደርና ለመስራት አሁንም ዝግጁ መሆኗን አስገዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለግብፅና ለሱዳን እንዲሁም ለተፋሰሱ ሀገራት መንግስታት በሙሉ መስከረም ላይ ሕዳሴ ሲመረቅ የደስታችን ተካፋይ እንዲሆኑ በይፋ ጋብዘዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ