ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ናት የባሕር በር ተጠቃሚ ካልሆነች ግን ሀገር መሆን አትችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ናት የባሕር በር ተጠቃሚ ካልሆነች ግን ሀገር መሆን አትችልም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በዛሬው ዕለት በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው።
በማብራሪያቸውም የቀይ ባሕር ጉዳይ ለሁሉም ጥቅም ሲባል በሰላማዊ መንገድና በንግግር ይሆናል፤ ኢትዮጵያ ሰላም ካጣችና ከተጎዳች ከኢትዮጵያ ያላነሰ ጎረቤት ሀገራት ይጎዳሉ ሲሉም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ናት፤ የባሕር በር ተጠቃሚ ካልሆነች ግን ሀገር መሆን አትችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም በእነሱ ወገን መከበር አለበት ብለዋል።
እኛም እንዳንጎዳ እነሱንም ሉዓላዊነታቸውን እናከብራለን በማለት ኤርትራ ሉዓላዊ ሀገር እንደሆነችና እኛም በግድ የኢትዮጵያ አካል እንድትሆን አንፈልግም ሲሉም አስገንዝበዋል።
አብሮ ለመኖር ያለው ነገር ሰጥቶ መቀበል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ በሰጥቶ መቀበል መርህ ንግግር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በትናንሽ ጠጠር አትበተንም ትልቅ ባሕር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የሚያውኳትን ተከላክላ መልማት የምትችል ትልቅ ሀገር ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚ፣ የህዝብ ቁጥር፣ የዘመነ ሰራዊት ያላት ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ከኤርትራ ጋር የጦርነት ስጋት ለሚያነሱ አካላት በእኛ በኩል ምንም ዓይነት ውጊያ እንደማንፈልግ ማወቅ ይገባል፤ ይህንን በእነሱም በኩል ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
በአድማሱ አራጋው
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!