የሀገር ውስጥ ዜና

ለዋጋ ግሽበት መፍትሔ ምርታማነትን ማሳደግ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

July 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዋጋ ግሽበት መፍትሔ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሆነና ለዚህም በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

የፊስካል፣ የገንዘብ ፖሊሲ እና የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ላይ የተወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በዚህም የዋጋ ግሽበት መቀነስ መቻሉን አንስተዋል።

የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 22 ነጥብ 8 በመቶ ዘንድሮ ወደ 14 ነጥብ 4 በመቶ ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።

የዋጋ ግሽበት መፍትሔ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሆነ በማንሳት ምርታማነት አድጎ የገበያ ትስስር እንዲጠናከር፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ1 ሺህ 400 በላይ የሰንደይ ማርኬት ማዕከሎች ማስፋፋት መቻሉን ተናግረዋል።

የዋጋ ግሽበት እድገት ምጣኔው ቀንሷል ማለት የሸቀጥ ዋጋ ቀንሷል ማለት እንዳልሆነ እና የዋጋ ግሽበት ምጣኔ ከሸቀጥ ዋጋ ጋር ተመጋጋቢ እንጂ ተመሳሳይ ጉዳዮች አለመሆናቸውንም አስረድተዋል።

ጤናማ የሆነ የዋጋ ግሽበት ለሀገር እድገት አስፈላጊ እንደሆነና ይህም በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እስከ 10 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ግሽበት ተቀባይነት ያለው በመሆኑ ወደዚያ ደረጃ ማውረድ እንደሚገባ አብራርተዋል።

በዚህ ጊዜ ደመወዝተኞች እና እጅ አጠር ሰዎች ተጎጂ እንደሚሆኑ ገልጸው÷ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ሀገሪቱ ከሰበሰበችው 900 ቢሊየን ብር ውስጥ 350 ቢሊየኑን ለድጎማ እንዲውል መደረጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሰራተኞች የተገኘው ውጤት እና የልማት ስኬት ተሸካሚ መሰረት በመሆናቸው እነርሱን የዘነጋ ልማት መታሰብ የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የዋጋ ግሽበትን ከፍላጎት ጋር ማጣጣም የሚቻለው እያንዳንዱ ግለሰብ ለፍላጎቱ የሚመጥን ገቢ ማመንጨት ሲችል ብቻ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያለው የደመወዝ መጠን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሲነፃጸር ሊያንስ እንደሚችል አንስተው÷ ኢትዮጵያን ካለችበት ለማውጣት፣ የተረከብነውን እዳና ስብራት ዋጋ በመክፈል ልጆቻችን እንዳይለምኑ ለማድረግና መከራን ለመቀበል ዝግጁ መሆን ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በዮናስ ጌትነት