የሀገር ውስጥ ዜና

የፖለቲካ ሀሳብን በምርጫ እንጂ በጠመንጃ ማሳካት አይቻልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

July 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ ሀሳብን በምርጫ እንጂ በጠመንጃ ማሳካት አይቻልም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጨቶችን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በምላሻቻውም በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ግጭቶች ዋነኛ ምክንያታቸው ሰነፍ ፖለቲከኞች እና ፍላጎትን በሀይል ለማስፈጸም የሚሞክሩ ሀይሎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህ ሀይሎች እንደ ድሮ መሳፍንቶች ሳይሰሩ ለመብላት ፍላጎታ እንዳለቸው አንስተው፤ እነሱ በሚሰጡት ተገቢነት የሌለው ትችት እና የተሳሳተ መረጃ ህዝቡን መደናገር ውስጥ እንደሚከቱት ገልፀዋል፡፡

አውርቶ አደሮች ዋናው ሃሳባቸው አባልቶ መብላት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ሰነፍ ፖለቲከኞች የሚጠቀሙት በዋናነት ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ወይም ሰላምን በማደፍረስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፍላጎትን በሀይል ለማስፈፀም የሚሞክሩ ሀይሎች የግጭት መንስኤ መሆናቸውን ገልጸው፤ እነዚህ ሀይሎች በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

እነዚህ ሀይሎች ሀይልን በበላይነት መጠቀም የሚችለው መንግስት መሆኑን የማይቀበሉ እንደሆኑ አስረድተው፤ የፖለቲካ ሀሳብን በምርጫ እንጂ በጠመንጃ ማሳካት አይቻልም ብለዋል።

በትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ሀይሎች የሰላም አማራጭን ቀዳሚ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

እነዚህን ሀይሎች ማህበረሰቡ በቃችሁ ሊላቸው እንደሚገባ ገልጸው፤ በተለያዩ ጊዜያት ህዝቡ የአጥፊ ሀይሎች እኩይ ተግባር በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መውጣቱን አስታወሰዋል፡፡

መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ለአፍራሽ ሀይሎች ምቹ እድልን የሚፈጥረውን ድህነት እና ኋላቀርነት ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ማህበረሰቡ ሳይሸሽግ የታጠቁ አካላትን አትግደሉ፣ አትግደሉልኝ፣ እናንተም አትሙቱልኝ ማለት አለበት ሲሉ ገልጸው፤ ልጆቼን ፈተና እንዳይፈተኑ እንዳይማሩ አትከልክሉ፣ እንዳንሰራ አታድርጉ፣ ማዳበሪያ እንዳይመጣ አታድርጉ ማለት አለበት ነው ያሉት።

በሚኪያስ አየለ