አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 42ኛ መደበኛ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡
ምክር ቤቱ በስብሰባው የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በዚህም የፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊየን ብር ሆኖ ጸድቋል፡፡
የ2018 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የፊሲካል ፖሊሲን ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል፣ የመንግስት ብድር ጤናማ እንዲሆን ከአበዳሪዎች ጋር የዕዳ ሽግሽግ ድርድር ማድረግ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስ የማህበራዊ ወጪ ድጎማን ማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰሩ ተጠቁሟል።
በጀቱ ከ2017 በጀት አንጻር የ34 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ያለው ሲሆን፤ ወጪው የሚሸፈነው ከ80 በመቶ በላይ ከሀገር ውስጥ ገቢ ሲሆን አዳዲስ የታክስ ምንጮችን ወደ ገቢ ስርዓቱ በማስገባትና የነበሩትን በማጠናከር ገቢን ለመጨመር እንደሚሰራ ተመላክቷል።