አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሊቨርፑል የፊት መስመር ተጨዋች ዲያጎ ዦታ እና በወንድሙ ድንገተኛ ህልፈት በርካታ የስፖርቱ ከዋከብቶችና የዓለም የስፖርት ቤተሰቦች ሀዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
የብሔራዊ ቡድን አጋሩ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፥ በተጫዋቹ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡
ከዦታ ጋር ከሳምንታት በፊት አብረን ነበርን ያለው ፖርቹጋላዊው ኮከብ፥ ዛሬ የተፈጠረውን ግን ለማመን ይከብዳል፥ ለባለቤቱ ለልጆቹ፣ ለቤተሰቦቹ እንዲሁም ለአድናቂዎቹ መፅናናትን እመኛለሁ ሲል የሀዘን መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
በተመሳሳይ የቀድሞው የሊቨርፑል አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ በዲያጎ እና በወንድሙ አንድሬ ጆታ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማኝ ሀዘን ጥልቅ ነው ብለዋል፡፡
ዲያጎ ምርጥ ተጨዋች ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡንና ትዳሩን የሚያከብር ጥሩ ጓደኛና መልካም ሰብዕና የነበረው ተጫዋችም እንደነበር ነው ክሎፕ የገለጹት፡፡
ክለቡ ሊቨርፑልን ጨምሮ የክለብ አጋሮቹ፣ የባርሴሎናው ኮከብ ላሚን ያማል፣ ሩብን ኔቬሽ፣ ሃሪ ማጓየር፣ ዴቪድ ዴሂያ፣ ዲክላን ራይስ፣ ፔድሪ፣ በርናርዶ ሲልቫ፣ ሜሰን ማውንት፣ ቨርጂል ቫንዳይክ፣ ፔፔ፣ አርሊንግ ሃላንድና ሌሎች በርካታ ተጨዋቾች በጆታ ህልፈት ሀዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
ተጨዋቹን ለማስታወስ በርካታ የሊቨርፑል ደጋፊዎች የተጨዋቹን 20 ቁጥር መለያ እና የአበባ ጉንጉን ይዘው በመውጣት ሀዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
የ28 አመቱ ፖርቹጋላዊ አጥቂ በዛሬው ዕለት በመኪና አደጋ በድንገት ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል፡፡
ዦታ በሰሜን ምዕራብ ስፔን ዛሞራ በተባለው ስፍራ እያሸከረከረ በነበረበት ወቅት ባጋጠመው የመኪና አደጋ ነው ህይወቱ ማለፉ የተገለጸው፡፡
በሚኪያስ አየለ